እንኳን ለ130ኛው የዐድዋ የድል በዓል አደረሰን። ዐድዋን ኢትዮጵያዊያን ፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እንዲሁም መላው አፍሪካዊያን ፣ ወደ ፊት ደግሞ የሰው ልጆች ሁሉ (ሰው እኩለነቱን ይማርበታልና) ሊያከብሩት የሚገባ ጋናና እና አኩሪ ታሪክን የያዘ የነጻነት ተጋድሎ እና የድል በዓል ነው።
በልጅነቴ ካነበብኳቸው ፣ የአተራረካቸው ለዛ ከሚማርከኝ ከተክለ ጻድቅ መኩሪያ “ዐፄ ምኒልክ እና የኢትዮጵያ አንድነት” መጽሐፍ ውስጥ በወፍ በረር አሳጥሬ የያዝኩትን ከተለያዩ ምንጮች ከተገኙ የፎቶግራፍ መዝገቦች ጋር እነሆ…

ንጉሥ ምኒልክ ከቴዎድሮስ ካመለጡ በኋላ ፣ መጀመሪያ ወደ ወሎዋ ገዥ ወደሆነችው ወደ ወርቂቱ በኋላም ወደ ትውልድ ሀገራቸው ወደ ሸዋ ሄደዋል። ንጉሥ ምኒልክ በዐፄ ቴዎድሮስ ተማርከው ሲሄዱ ሸዋን እንዲያስተዳደር በዐፄ ቴዎድሮስ የተሾመው በዛብህ ምኒልክን ወደ ሸዋ ላለማስገባት አንገራግሯል።
ንጉሥ ምኒልክ ወደ ሸዋ ከገቡ በኋላ ግዛታቸውን በማስፋፋት እና በማጠናከር ተጠምደዋል። በዐፄ ቴዎድሮስ ዘንድ በነበሩበት ጊዜ የፈረንጆቹን ብልኃት በመረዳታቸው ግንኙነት ለመፍጠር እና የእነሱን ብልኃት ወደ ሀገራቸው ለማስገባት ፍላጎት ነበራቸው። በተለይም የጦር መሣሪያ ለማስገባት ብዙ ጥረዋል። ከነዚህም ውስጥ ዋነኛው ከኢጣልያ መንግሥት ነው። ለዚሁም ከኢጣልያ መንግሥት ጋር ፔትሮ አንቶነሊ በተባለ የኢጣልያ መንግሥት ተወካይነት በ1880 የስምምነት ውል ተዋውለዋል። ውሉ የንጉሥ ምኒልክን እና የኢጣልያን መንግሥት የወዳጅነት ቃልኪዳን
- የኢጣልያ መንግሥት ንጉሥ ምኒልክን በመሣርያም ሆነ በሌላ ጉልበታቸውን ለማጠንከር ርዳታ ያደርጋል ፣
- ንጉሥ ምኒልክም በበኩላቸው የኢጣልያን መንግሥት ይረዳሉ ፣
- የኢጣልያ መንግሥት የኢትዮጵያን መሬት የትም ቦታ እንዳይነኩ ፣
- የኢጣልያ መንግሥት አሰብ ላይ ለሚገኝ የንጉሥ ምኒልክ ተወካይ 5ሺ ጠመንጃ ያስረክባሉ ፣
- ንጉሥ ምኒልክም በበኩላቸው እኒህን ጠመንጆች የኢጣልያ ሰዎችን ለመውጋት እንዳያውሉ እውነተኛ ቃል ይሰጣሉ ይላል።
ዐፄ ዮሓንስ መተማ ላይ የወደቁበትን እና ከርሳቸው በኋላ የነበረውን በመኳንንቱ መካከል የነበረውን መሸካከር እና የሥልጣን ሽግግሩን ጊዜ እንደ መልካም አጋጣሚ የተጠቀመው ጣሊያን የሀገሪቱን የቀይ ባሕር ጠረፍ ኤርትራ በሚል ስያሜ ይዟል። በዚህ ዘመን የነበረው የጣሊያን ጠቅላይ ሚንስቴር የሲቺሊያው ፍራቸስኮ ክሪስፒ ነበር። ከዐፄ ዩሓንስ ኅልፈት በኋላ ጣሊያኖች የትግራይ መኳንንት ቆመው አይመክቱንም ከንጉሥ ምኒልክ ጋር ስምምነት አለን ብለው አስበዋል። ምኒልክ ቢያንገራግሩም ደግሞ ሌሎች መኳንንትን እናስነሳባቸዋለን በሂደቱም ለኢጣልያ ሰፊ ግዛት እናገኛለን ብለው አስበዋል።

በዚህ ጊዜ ሁሉ ከዐፄ ምኒልክ ያልተለየው ኮንት አንቶነሊ የኢጣልያ መንግሥት የርሳቸው ወዳጅ እንደሆነ ፣ ጥቅማቸውን እንደሚጠብቅ ፣ የገንዘብ ብድርም ሆነ የጦር መሣሪያ ለማግኘት ግን በይፋ የስምምነት ውል ሲደረግ እና የኢትዮጵያ ዋና መልዕክተኛ ሮማ ሄዶ ከኢጣልያ ንጉሥ ጋር ሲገናኝ ነው በማለት ወትውቷቸዋል። በዚሁም ከሮማ የተላከለትን የውል ረቂቅ በግራዝማች ዮሴፍ (ፈረንሳይኛ የሚችሉ) ወደ አማርኛ ተተርጉሞ ለንጉሡ ቀርቦ ምክር እና መለስተኛ ጥናት ከተደረገበት በኋላ በ20 አንቀጽ የተከፈለውን የውጫሌን ውል ተፈራራሙ። ነገር ግን የአማርኛው ትርጉም እና ጣሊያንኛው ልዩነት ነበራቸው። ከነዚህም ውስጥ የ17ኛ አንቅጽ ልዩነት ለዓድዋ ጦርነት ምክንያት ሆኗል።
የአንቅጽ 17 አማርኛው
“የኢትዮጵያ ንጉሠ ነግሥት ከአውሮፓ ነገሥታት ጋር ለሚፈልጉት ጉዳይ ሁሉ በኢጣልያ መንግሥት አጋዥነት መላላክ ይቻላቸዋል።” ሲል የዚሁ አንቀጽ ጣሊያንኛው ደግሞ
“የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ከአውሮፓ ኃያላን ወይም መንግሥታት ጋር ለሚዋዋሉት ጉዳይ ሁሉ በግርማዊ የኢጣልያ ንጉሠ ነገሥት (አማካይነት) ለመጠቀም እሺ ብለዋል” የሚል ነው።
በ1885 እኤአ አፍሪካን ለመከፋፈል በበርሊን በተደረገው ስምምነት መሠረት ክሪስፒ ውሉን አባሪ አድርጎ ደብዳቤ በመላክ ውሉ በይፋ እንዲታወቅለት አድርጓል። ከተላከላቸው ሀገራት እንደ ፈረንሳይ ፣ እንደ መስኮብ እና ቱርክ ያሉት ሀገራት እንደ ኢትዮጵያ ነጻ ሆኖ የኖረ ሀገር የሌላውን ሀገር የበላይ ጠባቂነት በፈቃዱ እንዴት ይሰጣል በማለት በነገሩ ላይ ጥርጣሬ ስላደረባቸው ሁኔታውን ከአዲስ አበባ ለማጣራት ሲቆዩ ፣ ከጀርመን እና ከእንግሊዝ ግን እውቅና ተሰጥቶታል። ክሪስፒ ለዘለቄታ በኢትዮጵያ ላይ ጠባቂነትን ለኢጣልያ አስገኘሁ ብሎ በኢጣልያ ምክር ቤት ውስጥ ፎክሯል።
ዳግማዊ ምኒልክም በበኩላቸው የንግሥና ሥርዓታቸውን ከፈጸሙ በኋላ ፣ ለፈረንሳይ ፣ ለጀርመን እና ለእንግሊዝ ነገሥታት የዕወቁልኝ ደብዳቤ ልከዋል። ምላሹም በውጫሌ ከተዋዋሉት ውስጥ 17ኛውን አንቀጽ መሠረት በኢጣልያ መንግሥት ንጉሠ ነገሥት መሆንዎ ካልተላለፈለን አንቀበልም የሚል ነበር። ከነዚህ ነገሥታት ውስጥ ከጀርመን መንግሥት የመጣው ምላሽ ዐፄ ምኒልክን እና እቴጌ ጣይቱን አስቆጥቷል።
የኢጣልያ መንግሥት ዐፄ ምኒልክን በውል አፍራሽነት ለመወንጀል ተነሳስቷል። ዐፄ ምኒልክ ነገሩን በትዕግስት እና በሠላም ለመቋጨት በመፈለጋቸው ለኢጣልያ መንግሥት ስለሁኔታው የሚገልጥ ደብዳቤ ጽፈዋል።
ከጣሊያኑ ንጉሥ ከኡምቤርቶ ቀዳማዊ ፣ ይኸን ያደረግነው በሌሎች ኃያላን መንግሥታት ፊት የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስጠበቅ እንዲቻለን ስለወዳጅነታችን ነው የሚል አንድምታ ያለው እና ለዚሁም አመቺ እንዲሆን 17ኛውን አንቀጽ ተቀበሉ የሚል ምላሽ ተሰጥቷል።
እንዲሁም ቀደም ብሎ ኮንት አንቶነሊ ልዑክ ወደ ኢጣልያ እንዲልኩ ንጉሥ ነገሥቱን በወተወታቸው መሠረት ራስ መኮንን ከግራዝማች ዮሴፍ እና ከሌሎች መኳንንት ጋር ሄደው የደመቀ አቀባበል ተደርጎላቸው ነበር። እጅግ ትላልቅ ጥይቶችን የሚተኩሱ መድፎችን እንዲጎበኙ ተደርገዋል። ያረፉበትም ቦታ እጅግ የቅንጦት ቦታ ነበር። መስተንግዶው እንጎድቹን ለማስደነቅም ለማስደንገጥም ታቅዶ የተደረገ ይመስላል። በዚሁ ወቅት በኢጣልያ ጋዜጦች ላይ ሲወጣ የነበረውን የውጫሌ ስምምነት በተለይም አንቀጽ 17ን ያነበበው እና በወቅቱ ለትምሕርት ኢጣልያ ይገኝ የነበረው የዘጌው አፈወርቅ ስለነገሩ ክፉነት ለራስ መኮንን አሳውቋል።
ንጉሠ ነገሥቱ አንቀጽ 17 እንዲነሣ ካሳወቁበት ጊዜ ጀመሮ ጣልያኖቹ በመሸንገልም በማስፈራራትም ውሉ እንዲጸና ሞክረዋል። በተጨማሪም በጋዜጦቻቸው ዳግማዊ ምኒልክ ውል የማያከብሩ ፣ አገሪቱ ሥርዓት የማታውቅ ፣ ሕዝቡ ገና ካረመኔነት ያልተላቀቀ ፣ ሽፍታ እና የበሪያ ንግድ የሚያዘወትር ነውና ልናሰለጥነው ይገባል የሚል ፕሮፖጋንዳ ይነዙ ነበር።
ስለቀደመው የማደናገር ሥራው በወደ ኢጣልያ ተጠርቶ ሥልጣን የተሰጠው ኮንት አንቶነሊ ዐፄ ምኒልክን እንዲያግባባ እና በጣሊያንኛ የተጻፈውን ውል እንዲያስጸድቅ ወደ አዲስ አበባ ተልኳል።
ዐፄ ምኒልክ
- የውሉን 17ኛ ክፍል መሰረዝ
- በአማርኛ የተጻፈውን መቀበል
- በሁለቱም ቋንቋዎች የተጻፈውን እንዳለ መተው።
የሚሉ ሦስት ምርጫዎችን ሰጥተውታል።
ኮንት አንቶነሊ የጣሊያንኛው ለስምምነቱ ተቀባይነት ሊያገኝ ይገባል ብሎ መሟገቱን ቀጥሏል። ከብዙ ክርክር በኋላ ወደ ኢጣልያው ንጉሥ ኡምቤርቶ አንደኛ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት እና የኮንት አንቶነሊ ፊርማ ያለበት ደብዳቤ ጽፈው ለመላክ ይስማማሉ። በደብዳቤው አንቶነሊ የጣልያንኛው ቀርቶ የአማርኛው ይሁን ቢሉት ከንጉሤ እና ከጠቅላይ ሚንስቴሩ ሳላስፈቅድ አልችልም ስለማለቱ እና አሁን ግን 17ኛው አንቀጽ በፍጹም እንዲቀር መስማማታቸውን ጽፈዋል። ጽሑፉ ላይ የንጉሠ ነገሥቱ እና የኮንት አንቶነሊ ፊርማ ተቀምጧል።
አንቶነሊ በአማርኛ የተጻፈውን እና የፈረመበትን ከቤቱ ወስዶ ባስተርጓሚ ሲያስተረጉመው 17ኛ አንቀጽ እንዲሰረዝ መስማማቱን የሚገልጽ መሆኑን ተረዳ። በማግስቱ በንዴት ወደ ቤተመንግሥቱ ሄዶ 17ኛ አንቀጽ ይቅር አላልኩም ብሎ አመለከተ። ዐፄ ምኒልክም በግልጽ ባስተርጓሚ የተነጋገርንበትን ቢጸጽትህም አይለወጥም አሉት። በዚህ ጊዜ አንተ ነህ ይኸን ያደረኝኸው ብሎ ግራዝማች ዮሴፍን ተሳደበ። እቴጌ ጣይቱ “ቢያጠፋስ እኛ እንቀጣዋለን እንጅ አንተ ምን አግብቶህ ትሰድበዋለህ” ብለው ገሰጹት። ውጫሌ ላይ የተፈራረምነው የፈረንሳዩ ቃል ይታይ ሲል ፣ እኛ የምናውቀው የአማርኛውን ነው አሉት። በብስጭት ፣ ከእንግዲህ ወዳጅነት ቀርቷል ጦርነት ብቻ ነው በማለት ተሰርዟል የሚል ቃል ያለበትን ደብዳቤ ከፊታቸው ቀዶ ጣለው። እቴጌ ጣይቱ ከት ብለው በመሣቅ ጦርነቱን የዛሬ ሣምንት አድርገው በዚህ የሚደነግጥልህ የለም ብለው በቁጣ መልሰውለታል።

ኮንት አንቶነሊ ከዚህ በኋላ የሚፈይደው ነገር እንደሌለ አውቋል። ከሥራ ባልደረቦቹ ጋር ተመካክረው ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ወስነዋል። ይኸንኑ ውሳኔያቸውን ለዐፄ ምኒልክ በደብዳቤ አሳውቀዋል። ዐፄ ምኒልክም ያደረገው ድርጊት እንዳሳዘናቸው ፣ ለመሄድ ከቆረጡ እንደማይከለክሏቸው በጽሑፍ ገልጸውላቸዋል። እነ ኮንት አንቶነሊ ለመሄድ ውሳኔ ላይ በመድረሳቸው ነጉሠ ነገሥቱ ለጉዞ የሚያስፈልገውን ሰጥተው ወደ ሀገሩ ልከውታል።
ጣሊያኖች እንደ ሌሎቹ የአውሮፓ ኃያላን ቅኝ ቅዛት ለማግኘት የቋመጡ በመሆናቸውን የዐፄ ምኒልክን የሰላም መንገድ ከምንም አልቆጠሩትም ነበር። ይልቁንም ራስ መንገሻ እና ራስ አሉላ ፣ ሌሎችም መሣፍንት በዐፄ ምኒልክ ላይ እንዲነሱ ለማድረግ ጥረት ማድረጉን ተያያዙት። ከራስ መንገሻ ጋርም የተወሰነ ስምምነት አደረጉ። የጣሊያኖቹ እንቅስቃሴ ሊያስከትል የሚችለው አደጋ ለዐፄ ምኒልክ ታይቷቸዋል። አንቶነሊን ተክቶ ለመጣው የኢጣሊያ ተወካይ ወዳጃቸው የሆኑት ንጉሥ ኡምቤርቶ ይኸንን እንደማያደርጉ ምናልባት በምፅዋ የሚገኙ የበታች ሹማምንት አድርገውት ሊሆን እንደሚችል ይነግሩታል። ተወካዩ ከራስ መንገሻ ጋር ከተካሄደው ስምምነት ይልቅ ዐፄ ምኒልክን ወዳጅ መስሎ መያዝ አንቀጽ 17ን እንዲጸድቅ ማድረግ እንደሚቻል አስቧል። ይኸንኑ ሐሳቡን በኢጣሊያ የበላይ ሹማምንት ተቀባይነት እንዲያገኝ አድርጓል። በሂደቱም ጣሊያኖቹ ከራስ መንገሻ ጋር የገቡትን ስምምነት ማፍረስ ብቻ ሳይሆን አሰብ ላይ ይዘውት የነበረውን ዐፄ ምኒልክ የገዙትን 2 ሚሊዮን ጥይት ለዐፄ ምኒልክ ለቀውላቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ ከፈረንሳይ አዝዘው ሲጠባበቁ የነበረው 30 መድፍ ደርሶላቸዋል። በጣሊያኖች ክህደት የደረሰባቸው ራስ መንገሻ ጣሊያኖቹ ላይ አቂመዋል ፣ ከዐፄ ምኒልክ ጋር ታርቀዋል። ከዚህ በኋላ ዐፄ ምኒልክ በይፋ አንቀጽ 17 እንዲሰረዝ መጠየቅ ጀምረዋል።
ኢጣልያኖቹ አንቀጽ 17ን በማታለልም በማስፈራራትም ማጸደቅ አለመቻላቸውን ሲያዩ ፣ ለሌላ መንግሥት የጠባቂነት ስምምነት እንደማይሰጡ ቃል ይግቡልን እና ይሰረዝ ወደሚል ሐሳብ ሄደዋል። እቴጌ ጣይቱ ይኸ የኛ ጉዳይ እንጅ የኢጣልያ ምንግሥትን የሚያገባው አይደለም የሚል ሐሳብ ሰጥተዋል ፣ ንጉሡም ይኸንኑ የእቴጌ ጣይቱን ሐሳብ አጽድቀዋል።
ኢጣሊያን ወክለው ሐሳብ ሲያመላልሱ የነበሩት እነ ትራቬሲ በጻፉት መጽሐፋቸው በገጸበረከት እና በሽንገላ እናታልላለን ብለው ራሳቸው መታለላቸውን ፣ በዲፕሎማሲ መበለጣቸውን ፣ ምኒልክ ጥሩ ዲፕሎማት መሆናቸውን ጽፈዋል።
ራስ መንገሻም በተለያየ ምክንያት ሸፍተው ወደ ጣሊያኖቹ ገብተው የነበሩ የጦር መኮንኖችን ውስጥ ለውስጥ በመላላክ ከጣሊያኖች ጉያ ለማውጣት ጥረት አድርገዋል። በብዙ ተሳክቶላቸዋል። በተለይም ጣሊያኖቹን በሀገር ተወላጅ ላይ የሚያደርሱትን ግፍ እና ንቀት የተመለከቱት እና ቁጭት ያደረባቸው ወደ ወገናቸው ለመቀላቀል ከፍተኛ ፍላጎት አድሮባቸዋል።
ጣሊያኖችም ብዙ የኢትዮጵያ መኳንንትን ለማስከዳት እና እና በዐፄ ምኒልክ ላይ ለማሳመጽ ጥረት አድርገዋል ፣ ብዙ የሀገር ተወላጆችን በሰላይነት መልምለው አሰማርተዋል።
ጣሊያኖች ሐማሴንን እና አከለ ጉዛይን እያለፉ እስከ መረብ ድረስ ተጠግተዋል። እንደውም ውጊያ ብንገጥም ብዙ መኳንንት ይተባበሩናል ብለው አስበዋል። ይኸን የጣሊያኖቹን መስፋፋት የተመለከቱት ራስ መንገሻ ጦራቸውን ይዘው ከዓድዋ ወደ መረብ ተጉዘው አከለ ጉዛይ አውራጃ ገብተዋል። ጣሊያኖቹ ይኸንን እንዳወቁ ለጦርነት ተሰልፈዋል። በራስ መንገሻ እና በጣሊያኖች መካከል ኮአቲት ላይ ጦርነት ተካሂዷል። ራስ መንገሻ በቂ የስንቅ ዝግጅት አልነበራቸውምና ወደ ሰናእፈ ተመልሰው መስፈር ነበረባቸው ይባላል። ይኸም የኢጣልያን ጦር ሞራል ከፍ በማድረጉ ተከታትለው ራስ መንገሻን ለመውጋት ወስነዋል። ሊመሻሽ አካባቢ ሰናእፈ ደርሰው በራስ መንገሻ ላይ ጦርነት ከፍተዋል። የራስ መንገሻ ጦር ዝግጅቱ ስላልነበረው ቦታውን ለቆ ተበታትኗል። ይኸን ዜና ጣሊያኖቹ ለሮማ ሹማምንት እያጋነኑ ቴለግራም አድርገዋል። ከዚህ በኋላ የኢጣልያን ጦር የሚያቆመው የለም ብለው አምነዋል። የባራቲየሪ ዝና በኢጣልያ ገኗል።
በጄኔራል ባራቲየሪ እና በምክትሉ በጄኔራል አሪሞንዲ የሚመራው የኢጣልያ ጦር ወደ ዓድዋ ፣ ወደ መቀሌ እና ወደ አዲግራት ተንቀሳቅሰው በየከተማው የምሽግ ዝግጅት እና ሹም ሽር አድርገዋል። ጄኔራል አሪሞንዲ ጊዜያዊ የትግራይ አስተዳዳሪ ሆኖ ተሾሟል።
ከዚህ ቀጥሎ ጣሊያኖች ደብረ ኃይላ መድረሳቸው ታውቋል። የራስ መንገሻ ሹማምንት መክረው ራስ መንገሻ ወደ ራስ ወሌ ግዛት እንዲሄዱ ተወስኗል። ወታደሮቻቸው ግን ደብረ ኃይላ ላይ ለመመከት ወስነዋል። በማዦር አሜሊዎ የሚመራው ብዙ ያገር ተወላጆችን የያዘ ጦር የደብረ ኃይላን መንደሮች ማቃጠል ሲጀምር ፣ ከሸዋ ወደ ራስ መንገሻ ከሄዱት ከነቀኝ አዝማች ኃይለማርያም ጦር ጋር ገጥሟል። ጣሊያኖቹ የተሻለ የጦር ዝግጅት እና ወታደራቸውም በቁጥር ብዙ ስለነበረ ጦርነቱን አሸንፈዋል።
ከዚህ በኋላ በደረሱበት ሁሉ ሹም ሽር እያደረጉ ከደብረ ኃይላ አልፈው አላጌን ከዚያም አልፈው አሸንጌ ሐይቅን ይዘዋል። ከዚህ በኋላ …የምኒልክን ባላንጦች ማበረታታት አለብን…የሚል መልዕክት ለባራቲየሪ ደርሶታል። የኢጣሊያ መንግሥት የኢትዮጵያ መሣፍንትን እና መኳንንትን በምኒልክ ላይ ለማስነሳት ጥረት አድርጓል።

ይህ ሁሉ ሲሆን ፣ ዐፄ ምኒልክ ዲፕሎማሲያቸውን ሳያቋርጡ ለማይቀረው ጦርነት ዝግጅታቸውን ቀጥለዋል። ጣሊያኖች ወደፊት ገፍተው አዲግራትን እና መቀሌን ይዘዋል። ከዚያም አልፎ ግንባር ቀደሙ የኢጣልያ ጦር ወደ አምባ አላጌ መገሥገሡን በዐፄ ምኒልክ ዘንድ ተሰምቷል። ምኒልክ በመስከረም ወር 1888 የሚከተለውን የክተት ዐዋጅ ዐውጀዋል
እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ ፣ አገር አስፍቶ አኖረኝ። እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ። እንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉም ነውና ስለኔ ሞት አላዝንም። ደግሞም እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም። እንግዲህም ያሳፍረኛል ብየ አልጠራጠርም። አሁንም አገርን የሚያጠፋ፥ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባህር አልፎ መጥቷል። እኔም ያገሬን ከብት ማለቅ የሰውንም መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደ ፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር። አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም። ያገሬ ሰው! ካሁን ቀደም የበደልኩህ አይመስለኝም። አንተም እስካሁን አላስቀየምከኝም። ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበት የሌለህ ለምሽትህ፥ ለሃይማኖትህ፥ ለሀገርህ ስትል በሐዘን እርዳኝ። ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጠላኛለህ ፣ አልተውህም! ማርያምን! ለዚህ አማላጅ የለኝም! ዘመቻዬም በጥቅምት ነውና እስከ ጥቅምት እኩሌታ የሸዋ ሰው ወረኢሉ ከተህ ላግኝህ።
በራስ መኮንን አዝማችነት ግንባር ቀደም የሆነው ጦር ቀድሞ አላጌ ደርሷል። ራስ መንገሻም ጦራቸውን ይዘው ተቀላቅለዋል። በማዦር ቶዜሊ የሚመራው የኢጣልያ ጦር (ብዙ የሀገር ተወላጆች ያሉበት) አምባ አላጌ ላይ መሽጓል። ራስ መኮንን ነገሩን በሠላም ለመቋጨት ከጣልያን መኮንኖች ጋር ደብዳቤ ተጻጽፈዋል። ሂደቱ ግን ርባና ያለው ውጤት አላስገኘም ነበር። ራስ መኮንን ከቶዘሊ ጦር ጋር በታሕሳስ ሰባት 1888 ዓም ገጥመው የቶዜሊን ጦር ድል አድርገዋል። በጦርነቱም ማጆር ቶዘሊ ሕይውቱን አጥቷል። በጦርነቱ ላይ የራስ አሉላ እና የራስ መንገሻ ጦርም ተሳትፏል።
ከድሉ በኋላ አለ ትዕዛዝ ጦርነቱን የጀመሩት ፊታውራሪ ገበየሁ እና ቀኝ አዝማች ታፈሰ ታስረዋል። ለዐፄ ምኒልክም የድሉን ዜና በመልዕክተኛ አድርሰዋቸዋል። በዚህ ጊዜ ንጉሡ በውጫሌ ፣ በባሻ ጨፌ ፣ በመርሳ እና በጭራ ወንዝ አድርገው በኦላ ወንዝ እና በጎሊማ አድርገው ሆርማት ላይ ሰፍረው ነበር።
የአምባ አላጌው ድል ኢጣልያኖቹን ወደ ቀልባቸው አልመለሳቸውም። ይልቁንም ተደፈርን በሚል ስሜት ለበቀል ተነሳስተዋል። አዳዲስ ጦርም ወደ ኤርትራ ማስገባት ጀምረዋል። በግዳጅም ፣ በኩርፊያም ፣ በድለላም ከኢጣልያኖች ጋር በተሰለፉት የሀገር ተወላጆች ዘንድ ግን ወደ እናት ሀገራቸው ለመመለስ መነሣሣትን ፈጥሯል። ብዙዎች ወደ ራስ መኮንን ጦር እየመጡ ተቀላቅለዋል።
ዐፄ ምኒልክ በመንገዳቸው እየመጣ የሚቀላቀላቸውን ጦረኛ እየተቀበሉ ከአዲስ አበባ በተነሱ በሦስተኛው ወር መጀመሪያ ላይ በታኅሣሥ 5 ወፍላ በ8 አሸንጌ በ 11 1888 ደምባልአ ላይ ደርሰዋል። ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ከጎጃም ተነስተው በበጌምድር አድርገው ታኅሣሥ 15 ቀን ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር ተገናኝተዋል። በ19 እንዳ መሆኔ በ23 ዋጀራት ገብተዋል። በ26 ጨለቆት ሰፍረዋል። ቀድመው የነበሩት ራስ ሚካኤል ፣ ራስ ወሌ ፣ ራስ መንገሻ ዩሓንስ፣ ራስ መንገሻ አቲከም ፣ ራስ መኮንን ፣ ራስ አሉላ እና ራስ ወልዴ ወደ ኋላቸው ተመልሰው ከነጉሠ ነገሥቱ ጋር ጨለቆት ላይ ተገናኝተዋል። በ28 ገናን አክብረው በ29 ከጨለቆት ተነስተው መቀሌ ሰፈሩ።


| የጦሩ መሪ | ሲያንስ | ሲበዛ |
| ዳግማዊ ምኒልክ | 34000 | 38000 |
| እቴጌ ጣይቱ | 5000 | 6000 |
| ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት | 5000 | 6000 |
| ራስ ሚካኤል | 14000 | 15000 |
| ራስ መኮንን | 15000 | 16000 |
| ራስ ቢትወደድ መንገሻ | 5000 | 6000 |
| ራስ ወሌ | 6000 | 7000 |
| ራስ መንገሻ ዮሐንስ ፣ የራስ አሉላን እና የራስ ሐጎስን ጨምረው | 3000 | 4000 |
| ፊታውራሪ ገበየሁ | 13000 | 14000 |
| ድምር | 110 000 | 123 000 |
189000 ልዩ ልዩ ጠብመንጃ ፣ ሁለት ሚሊዮን አንድ መቶ አርባ አራት ሺ ጥይት ፣ 46 መድፎች
በሰላይነት የተያዘው መሐንዲሱ ካፑቺ ወደ 68 500 ዝቅ ያደርገዋል። በአሁኑ ጊዜ ግን ቁጥሩን እየጨመሩ እስከ 200 000 አድርሰውታል።



ከአላጌው ጦርነት በኋላ የንጉሠ ነገሥቱን ጦር መቀሌ መስፈር ያወቀው ወደ ሹማምንቱ ጦር እና የጦር መሣሪያ እንዲላክለት ጠይቋል። የሚፈልገውን ሁሉ እንደሚልክለት ቃል የገባው ጠቅላይ ሚንስቲሩ ክሪስፒ አገሪቱ አንድ ሌላ ድል ከአንተ ትጠብቃለች ፣ ይኸም ድል የሐበሻን ጉዳይ ለዘለቄታው የሚደመድም መሆን አለበት። የራስህ እና የኢጣሊያ ክብር ያለበት ነው የሚል መልዕክት አስተላልፎለታል።
ራስ መኮንን ዛሬም የሰላም አማራጩን ላለመዝጋት በመቀሌ መሽጎ ለሚገኘው ለጋልያኖ ቦታውን ለቆ እንዲሄድ እስከ ምፅዋ የሚያደርሰው ሸኝ እንደሚሰጡት የሚገልጥ ደብዳቤ ለክውበታል። እርሱም እምቢታውን እና የትዕቢት መልሱን መልሷል።
ጣልያኖቹ ተኩስ በመጀመራቸው ፣ ንጉሠ ነገሥቱ ባዘዙት መሰረት ሊቀመኳስ አባተ እና በጅሮንድ ባልቻ መድፍ እና መትረየሳቸውን ጠምደው ምሽጉን ይደበድቡት ጀመር።
ቢሆንም የኢጣሊያ ጦር ጥሩ ምሽግ መሽጎ ስለነበረ ብዙም ጉዳት አላደረሱበትም። በኋላ እቴጌ ጣይቱ ለጣሊያኖች አቅራቢያ የነበረውን እና ለመጠጥ ውኃ ይጠቀሙበት የነበረውን ምንጭ የራሳቸውን ወታደሮች አዘው አሲያዙት። ይህ ድርጊት የኢትዮጵያ ወታደሮችን ብዙ ሕይወት ሊያስከፍል ይችል የነበረውን የምሽግ መሥበር ውጊያ አስቀርቷል ፣ በውኃ ጥም ከሞት አፋፍ ላይ የደረሰው የኢጣሊያ ወታደር በትዕቢት ተወጥሮ የነበረው እና ቀድሞ ብዙ የደነፋው ማጆር ጋሊያኖ በውኃ ጥም ከማለቅ በንጉሡ መልካም ፈቃድ እና በራስ መኮንን ዋስነት ከምሽጉ ወጥቶ ወደ ወገኖቹ እንዲቀላቀል ሆኗል። ዐፄ ምኒልክም ለአንደኛው የኢጣልያ ሰው ከሀገራችሁ መምጣታችሁ የሰው ሀገር እንይዛለን ማለታችሁ ከጉድባ ውስጥ ገብቶ በውኃ ጥም ለማለቅ ነውን ፣ እኔ ግን የክርስቲያን ንጉሥ እንጅ የአሕዛብ ንጉሥ አይደለሁም… አሁንም ክርስቲያኖች በከንቱ አይለቁ ሰዎችህን ልከህ አስወስድ ትዋጉም እንደሆነ አንድነት ተሰብስባችሁ ጠብቁኝ እኔም እመጣለሁ ብለህ ለባራቲየሪ ንገረው አሉት።
ከዚህ በኋላ ጣሊያኖቹ ጦራቸውን እስከሚያደራጁ ፣ ምሽጋቸውን እስከሚያጠናክሩ ላይ ላዩን የእርቅ ወሬ ማውራት ጀምረዋል። ወደኋላ ላይ እብሪት የተሞላበት የመደራደሪያ ሐሳብ አቅርበዋል። የመደራደሪያ ሐሳቡ በአጭሩ ሲቀመጥ
- የውጫሌ ውል ታድሶ እንዲረጋ ፣
- የኢጣሊያ ባንዲራ እስከተሰቀለበት ያለው ሀገር የኢጣልያ እንዲሆን
የሚል ነው።
ዐፄ ምኒልክ ጦራቸውን ከመቀሌ አንስተው ወደ ሐውዜን ፣ ከሐውዜን ወደ ፈረስ ማይ ፣ ከፈረስ ማይ ወደ ሳውርያ ከዚያም ወደ ዐድዋ ታጥፈው የጦር ሰፈራቸውን የሐ የሚባለው ሥፍራ አድርገዋል።
በዚሁ ጊዜ ከራስ መንገሻ ጋር በነበራቸው ጠብ ለጣሊያኖች ገብተው የነበሩት ራስ ስብሐት እና ደጅ አዝማች ሐጎስ ተፈሪ ወደ ኢትዮጵያ መንግሥት ጦር ተቀላቅለዋል።
የኢትዮጵያ ሠራዊት ስንቅ የሚያጓጉዘው በባህላዊ መንገድ (ከዋናው የስንቅ መስፈሪያ ከቦሩ ሜዳ እና ከወረኢሉ ነው።) ወታደሩ ለብዙ ወራት በመንገድ በመቆየቱ ወታደሩ ሳይዋጋ ወይም ነገሩ በሠላም ሳይቋጭ ብዙ ለመቆየት የሚያስችለው ሀብት አልነበረም።
ጣልያኖቹ ምሽግ ሰርተዋል ፣ ከምሽጋቸው ምቾት ሆነው ጦርነቱን ሊያደርጉ ይፈልጋሉ። በተለይም የሀገር ተወላጆች ወደ ራሳቸው (ወደ ኢትዮጵያዊያን) ኃይል በመቀላቀላቸው ጦርነቱን ለመከላከል ሲቻል ለማዘግየት እንጅ ከምሽግ ወጥተው ለመዋጋት መነሣሣቱ አልነበራቸውም። ኢትዮጵያዊያኑን በመተንኮስ ለውጊያ የተሰለፉ መስለው መልሰው ወደ ምሽጋቸው በመግባት ፣ ኢትዮጵያዊያኑ ምሽጉን ለመስበር እንዲዋጉ ለማነሣሣት እና ከምሽጉ ውስጥ ሆነው በመድፍ እና በመትረየስ ፈጅተው በቀላሉ ድል ለማድረግ ብዙ ጊዜ ሞክረዋል።
ኢትዮጵያዊያኑም ጣልያኖቹ ከምሽጋቸው ወጥተው እንዲዋጉ ፣ የኢትዮጵያ ሠራዊት ምግብ አልቆበት ለዘረፋ ተበትኗል ፣ እነራስ እከሌ እነ ራስ እከሌ ከድተዋል የሚል ወሬ ጣሊያኖች ሰላይ አድርገው በላኳቸው ሰዎች በኩል ማድረስ ጀምረዋል። አንዳንዶቹ መኳንንት ጦርነቱን ብትጀምሩ ወደ እናንተ እንገባለን ብለው እስከመጻፍ ደርሰዋል። ይኸ ዘዴ ሰርቶ ጣሊያኖቹ ከምሽጋቸው ወጥተው ለመዋጋት ወስነዋል።
| መሪ | የወታደር እና የመድፍ ብዛት |
| የኢጣልያን ጦር በዋናነት የሚመራው ጄኔራል ባራቲየሪ | 5000 አካባቢ የሚሆኑ ወታደሮች |
| ጄኔራል ዳቦርሜዳ | 3800 ወታደር 18 መድፍ |
| ጄኔራል አሪሞንዲ | 2493 ወታደር 12 መድፍ |
| ጄኔራል አልቤርቶኒ | 4076 ወታደር 14 መድፍ |
| ጄኔራል ኤሌና | 4150 ወታደር 12 መድፍ |

ከዚህ ድል በኋላ በጄኔራል አልቤርቶኒ የዤኒራል አሪሞንዲ እና የዤኒራል ዳቦር ሜዳ ጦር ተሰልፎ ወጥቷል። ግንባር ቀደም ሆኖ የጀመረው በማዦር ቶሪ የሚመራው ጦር ነበር። ኢትዮጵያዊያኑ ስላየሉ ወደ ኋላው ሸሽቶ የአልቤርቶኒ የጦር ሰፈር ደርሷል። የኢትዮጵያዊያኑ ጦር እየተከታተለ ደርሶ ዋናው ጦርነት ተጀመሯል። የጀኔራል አልቤርቶኒ ጦር በመድፍ እና በመትረየስ አጥብቆ ተከላክሏል። የወታደሩን ማመንታት የተመለከተው ፊታውራሪ ገበየሁ የአምባላጌው አሸናፊ ፊት አውራሪ ገበየሁ በምን አኳኋን እንደሞተ ወደ ሸዋ በሕይወት የሚመለሱት ይናገሩ ብሎ ተናግሮ እንደ አንበሳ ተወርውሮ ወደ ጣሊያኖች መስመር ገብቶ 3 ሰዓት ላይ በመትረየስ ተመትቶ ኪዳነ ምሕረት እበሩ ላይ ወድቋል።
ንጉሡ ቀይ ዣንጥላቸውን አስዘርግተው ወደ ግንባሩ ዘልቀዋል። በአልቤርቶኒ የሚመራው የኢጣሊያ ጦር ሽሽት ጀምሯል። አልቤርቶኒ በፈረስ ሊሸሽ ሲል ፈረሱ ተመትቶ ወድቋል። ኢትዮጵያዊያኑ ደርሰው ማርከውታል። በዚሁ ጦርነት ራስ መኮንን እጃቸውን ቆስለዋል። ቁስላቸውን አስረው ውጊያውን ቀጥለዋል።
በጀኔራል አሪሞንዲ ጦር ፊትለፊት ለውጊያ የተሰለፉት ራስ ሚካኤል እና ራስ ወሌ ነበሩ። የጀኔራል አልቤርቶኒን ጦር የደመሰሰው የኢትዮጵያ ጦር በመካከል ሆነው ለሚዋጉት ለነራስ ወሌ ተደራቢ ሆኖ የአሪሞንዲን ጦር ገጥሞታል። ጄኔራል አሪሞንዲ እና ኮሎኔል ጋሊያኖ በዚሁ ጦርነት ላይ ሞተዋል።
ከዚህ ቀጥሎ ከሌሎቹ ተገንጥሎ በማርያም ሸዊት የነበረውን የዳቦርሜዳን ጦር ኢትዮጵያዊያኑ ደርሰው ከበው ገጥመውታል። ደቦርሜዳ እና ብዙዎቹ ተከታዮቹ በጦርነቱ ላይ አልቀዋል።
በወቅቱ የዐይን እማኝ የነበሩ ኢትዮጵያዊ ጸሐፊ እንደገለጡት…
የካቲት 23 ቀን ከሌሊቱ 11 ሰዓት አካባቢ የኢጣሊያ ጦር በድንገት ደረሰ። ጦርነቱ ተጀመረ። የኢትዮጵያ ወታደር ወንድሙ ሲወድቅ ወንድሙ እያነሳው ፣ ጥይቱ ያለቀበት ከቆሰለው ወገብ ላይ እየወሰደ ተኩሱን ይቀጥላል። እቴጌ ጣይቱ ጥቁር ጥላ አስይዘው ዐይነ ርግባቸውን ገልጠው ፣ በንጉሠ ነገሥቱ ልጅ በወይዘሮ ዘውዲቱ እና በደንገ ጡሮች ታጅበው ድሉ የኛ ነውና በለው እያሉ እንደ ወንድ ወታደሮቻቸውን አሰልፈው ወደ ጦርነቱ ገቡ።
የኢትዮጵያ ጦር ከጦርነቱ የሸሸውን የኢጣልያ ጦር እየተከታተለ ፣ የራቀውን በጥይት የቀረበውን በጦርና በጎራዴ እየመታ ፈጀው። ዐፄ ምኒልክ ወደፊት እየገፉ ጦር ያነሰበትን እየመረመሩ በፍጥነት እየላኩ ሲያዋጉ ዋሉ። የመጀመሪያው ድል የተፈጸመበት ቦታ እቴጌ መጥተው በእርኮት እና በገንቦ ያለውን ውኃ እና መጠጥ በገረዶች እያስቀዱ ቁስለኞቹን ኢትዮጵያዊያን እና ጣሊያኖቹም ሳይቀሩ እንዲጠጡ እና እንዲረኩ አደረጉ።
9 ሰዓት አካባቢ ያፄ ምኒልክ ጦር ምርኮ እየያዘ ሲመለስ ንግሥቲቱ ፣ ንጉሡ ሳይመለሱ ወዴት ነው የምትመለሰው ምርኮኛችሁን እየሰጣችሁኝ ወደዚያው ተመለሱ ብለው ጮሁባቸው። ዐፄ ምኒልክ ወደ ሠፈር ሲመለሱ ጊዜው መሽቶ ነበር።
ጳጳሱ አቡነ ማቲወስ እና የቀሩትም መነኮሳት የሚያጣጥረውን በማናዘዝ ፣ የሚሸሸውን እንዲመለስ በመገዘት የመንፈስ አባትነት ሥራቸውን ተወጥተዋል።
- ከዐድዋ ድል ማግስት ምኒልክ የአውሮጫዊያንን ቀልብ ስበዋል
- የሎንዶን ታይምስ ድሉ እስካሁን በንቀት ሲታዩ የነበሩ የአፍሪካውያንን መንፈስ ያነቃቃል የምኒልክ ድል የመላው አፍሪካዊያን ድል ነው ሲል ጽፏል።
- የፓሪስ ዊክሊ ጋዜጣ የምኒልክን እና የጣይቱን ፎቶዎች በገጹ አትሟል።
- የኒውዮርክ ታይምስ ሐበሾች ኢጣልያን አሸንፈዋል የሚል ኅትመት አውጥቷዋል።
- የጦርነቱ ውጤት በኢጣልያ ሕዝብ ላይ የመሸበር እና የብስጭት ስሜት ጭሯል።
- በመንግሥቱ ላይ አምጿል ፣ ቪቫ ምኒልክ ብሏል ፣ የክሪስፒ ሥርዓተ መንግሥት በመጋቢት 5 1896 ፈርሷል።
- የእንግሊዝ የቅኝ ግዛት እና የውጭ ጉዳይ ቢሮዎች ምኒልክ በሶማሌ እና በሱዳን ያሉ የእንግሊዝን ንብረት ሊያጠቃ ይችላል ብለው ፈርተዋል።
- በጥቅምት 23 1896 የኢትዮ ኢጣሊያን ጦርነት መጠናቀቅ በደንብ የሚያበስር ስምምነት በአዲስ አበባ ተፈርሟል።
- የውጫሌ ውል ተሰርዞ ኢጣልያ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ተቀብላለች።
- ኢጣልያ ፓርላማቸው ከወሰነ ኤርትራን ለኢትዮጵያ ለመመለስ ተቀብላልች።
- በግንቦት 22 1897 የኢጣልያ ባለሥልጣናት በ222 ተቃውሞ እና በ140 ተቀብሎ የኤርትራን መመለስ ውድቅ አድርገዋል።
- ኢጣልያ ላደረገችው የወረራ ጦርነት አፄ ምኒልክ 12 ሚሊዮን ሊሬ ካሳ ጥይቀዋል።
- በግ ንቦት 14 897 እንግሊዝ የኢትዮጵያን ሉ አላዊነት ተቀብላለች።
- እንዲሁም የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ከነበረችው የሶማሊያ ግዛት ጋር የነበረውን የድንበር ውዝግ እልባት ሰጥተዋል።
- የኢትዮጵያ የግዛት ድንበሮች በ1897 ከእንግሊዝ እና ከፈረንሳይ ጋር በ1900 ከኢጣልያ ጋር በ1904 ከ ሱዳን የእንግሊዝ/ግብጽ አስተዳደር ጋር ፣ በ1908 ከእንግሊዝ ኬን ያ አስተዳዳሪዎች ጋር በተደረጉ ስምምነቶች የተጠበቁ ሆነዋል።
- በቅኝ ግዛት ጭቆና ለነበሩ የአፍሪካ ሕዝቦች
- የትምክህት ፣ የተስፋ ፣ የመነሳሳት ምክንያት እና የነጻነት ምሳሌ ሆኖላቸዋል
- ዘረኝነትን ለመቀልበስ የእኩልነት ምሳሌ ሆኗል ፣ ከቅኝ ግዛት ቀንበር ለመውጣት በሚደረገው የምከታ ትግል ውስጥ ምልክት ሆኗል
- ለአፍሪካ የነጻነት ሐሳብ መነሻ ሆኗል
- አዲስ አበባን በ1904 የጎበኘ ቤኒቶ ሲልቫኒ የተባለ ሰው የፓናፍሪካዊነትን ሐሳብ አቀንቅኗል
- ቀይ ፣ ቢጫ ፣ አረንጓዴ ቀለማት የፓናፍሪካዊነት ቀለማት ሆነው ተመርጠዋል
- ብዙ የአፍሪካ ሀገራት ሰንደቅ ዓላማቸው ከቀይ ፣ ቢጫ ፣ አረንጓዴ ቀለማት ቀምረዋል።

የዐድዋ ጀግኖች የነጻነት መንፈስ ይደርብን ፣ አሜን
