የመጽሐፈ አክሲማሮስ ሥነቁስ

(ከግምት ነጻ ለመሆን የሚደረጉ የዕውቀት ምርመራዎች አሉ ፣ ከትግበራቸው ውጤት ለኑሮ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለማሟላት የሚደረጉ እንዲሁ አሉ። ይኸ ከመጀመሪያው ዐይነት ይመደባል። …)

የሰው ልጅ አካባቢውን ለመረዳት ብዙ ጥሯል ፣ በዚህ ረገድ ብዙ ርቀት ተጉዟል።

ቁስ ከማይታዩና ከማይከፋፈሉ ጠጣር ድቡልቡል አተሞች የተዋቀረ ነው ፣ ብዙ አተሞች አሉ ፣ ሜካኒካዊ ሕግ ብቻ የሚከተሉና ርስበርሳቸው በብዙ ዐይነት መንገድ የተሳሰሩ ናቸው የሚል መላ ምት የነበረው የአብደራው ዴሞክሪተስ (ዴሞክሪተስ ዘአብደራው ) ነበር ይባላል ። ተቀራራቢ ሐሳብ የሚያቀነቅኑ ጥንታዊ ማኅበረሰቦች ነበሩ። አተማዊያን (atomists) ይባላሉ። አስተሳሰቡ ደግሞ አተማዊነት (atmoism) ይባላል።

የአተማዊያን አስተሳሰብ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት ባይኖረውም ፣ ዘመናዊ ሳይንስም መጠናቸው እጅግ ትንሽ የሆነ[1] መሠረታዊ የሆኑ መሥራች ቅንጣቶች እንዳሉ ይቀበላል (Dalton, Wollaston, & Thomson, 1893)። ለነዚሁ ቅንጣቶች ፣ አተም የሚለውን ስያሜ ጥቅም ላይ አውሏል። ነገር ግን የዘመናችን ሳይንስ አተም ያላቸው መሠረታዊ ቁስ አካላት ቀደምት እንዳተቱት የማይከፋፈሉ አይደሉም። ኤሌክትሮን[2] ፣ ፕሮቶን[3] እና ኒውትሮን[4] ከሚባሉ አተም መሥራች ቅንጣቶች ፣ ትኅተ አተም ቅንጣቶች (subatomic particles) የተዋቀሩ ናቸው ይላሉ። ይኸ የዘመናችን ሳይንሳዊ እሳቤ መሠረት ሆኖ እንደቀጠለ ነው።

በሀገራችን ተተርጉመው ከሚገኙ ቀደምት የሥነ-ቁስ ሐተታዎች በመጽሐፈ አክሲማሮስ የሚገኘውን እንመልከት (መጽሐፈ አክሲማሮስ-ዘስድስቱ ዕለታት, ፲፱፻፺፱ ዕትም)። አክሲማሮስ በ15ኛው መቶ ክፍለዘመን? ከዐረብኛ ወደ ግእዝ የተተረጎመ መጽሐፍ ሲሆን የስድስቱን የፍጥረት ዕለታት የአፈጣጠር ሂደት የሚናገር መጽሐፍ ነው። የአክሲማሮስ ፀሐፊ ኢፒፋኒዮስ ነው ይባል እንጅ ፀሐፊው በውል አይታወቅም ይላሉ። (ኢፒፋኒዮስ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረ ከአበው ክርስቲያኖች አንዱ እና የቅድስና ማዕረግ የተሰጠው አባት ነበር።)

የመጽሐፉን የተወሰኑ ሐሳባት ከግእዝ ወደ አማርኛ ከተተረጎመው መጽሐፍ ላይ የማንበብ ዕድል አጋጥሞኛል። መጽሐፉ የምናያቸው ፍጥረታት ሁሉ ከአራት ባሕርያት የተገኙ እንደሆኑ ያትታል። እነዚህም እሳት ፣ ነፋስ ፣ ውኃ እና መሬት ናቸው ይላል። ይኸን አስተሳሰብ በአሪስጣጣሊስ የፍልስፍና መጽሐፍ ላይም እናገኘዋለን።

የባሕርያቱን ጠባዊ ዝምድና ሲገልጥ

«እሳት ውኃን ያፈላዋል ፣ ውኃ እሳትን ያጠፋዋል ፣ ንፋስ መሬትን ይበትነዋል ይዘረዝረዋል ፣ መሬትም ነፋስን ይገድበዋል ፣ ነፋስ ውኃን ያማታዋል ፤ እንደከበሮ ያስጮኸዋል።»

በተጨማሪም መጽሐፉ እያንዳንዳቸውን ባሕርያት ሦስት ሦስት ግብር ይሰጣቸዋል። እነዚህም

  • እሳት — ብሩኅነት፣ ሞቃትነት፣ ደረቅነት
  • ነፋስ — ሞቃትነት፣ ቀዝቃዛነት፣ ጥቁርነት
  • ውኃ — ብሩኅነት፣ ቀዝቃዛነት፣ ርጥብነት
  • መሬት — ደረቅነት፣ ጥቁርነት፣ ርጥብነት

እንደዚሁም «ብርሃን ከእሳት የተገኘ ነው። ጨለማ ከበርባሮስ ነው።» ይላል።

እንዲሁም መጽሐፈ አክሲማሮስ እያንዳንዱ ግብር (ቅስም) በሁለት ንጥረ ነገሮች የተያዘ በመሆኑ እያንዳንዳቸው ንጥረ ነገሮች ከቀሪዎቹ ሦስቱ ጋር የሚያመሳስላቸው (የሚያዋድዳቸው) አንዳንድ ባሕርይ እንዲኖራቸው ያደርጋል።

  • እሳት:
    • ከውኃ ጋር በብሩኅነት
    • ከነፋስ ጋር በሞቃትነት
    • ከመሬት ጋር በደረቅነት
  • ነፋስ:
    • ከእሳት ጋር በሞቃትነት
    • ከውኃ ጋር በቀዝቃዛነት
    • ከመሬት ጋር በጥቁርነት
  • ውኃ:
    • ከእሳት ጋር በብሩኅነት
    • ከነፋስ ጋር በቀዝቃዛነት
    • ከመሬት ጋር በርጥብነት
  • መሬት:
    • ከእሳት ጋር በደረቅነት
    • ከውኃ ጋር በርጥብነት
    • ከነፋስ ጋር በጥቁርነት

በዚህ አካሄድም አክሲማሮስ የሚታየው ዓለም መሠረቱ ቅስማዊ ባሕርያት (qualities) ናቸው የሚል ዕይታን የያዘ ነው። ይኸም አስተሳሰብ ቢሆን በአሪስጣጣሊስ ፍልስፍና ውስጥ ከሚገኘው የተቀራረበ ነው። ለምሳሌ አሪስጣጣሊስ ሙቅነት እና ቀዝቃዛነትን ፣ ደረቅነትን እና ርጥንበትን እንደ መሠረታዊ የአራቱ ባሕርያት ቅስማዊ ግብር አድርጎ አቅርቧቸዋል (እሳት፡ ሞቃትነት እና ደረቅነት ፣ ነፋስ፡ ሞቃትነት እና ርጥብነት ፣ ውኃ፡ ቀዝቃዛነት እና ርጥብነት ፣ መሬት፡ ቀዝቃዛነት እና ርጥብነት)። በመጽሐፈ አክሲማሮስ ብሩኅነት እና ጥቁርነትን በመጨመር እያንዳንዳቸው ንጥረ ነገሮች ሦስት ሦስት ባሕርያት እንዲኖራቸው ከማድረጉ በተጨማሪ ፣ የነፋስ እና የመሬት ግብሮች ላይ የተወሰነ ለውጥ አድርጓል። ይኸውም

  • ነፋስን አሪስጣጣሊስ ሞቃትነትን እና ርጥበትን ሲሰጠው ፣ አክሲማሮስ ግን ቀዝቃዛነትን ፣ ሞቃትነትን እና ጥቁርነትን በመስጠት ነፋስ የሙቀት ብቻ ሳይሆን የሙቀትም የቅዝቃዜም አስተላላፊ አድርጎታል ፣ በጥቁርነቱም ብርሃን የማይሰጥ እንደሆነ ያጠቁማል።
  • አሪስጣጣሊስ መሬትን ቀዝቃዛነት እና ርጥብነት አለው ሲል አክሲማሮስ ደግሞ ደረቅነትን ርጥብነትን እና ጥቁርነትን በመስጠት የርጥበት አስተላላፊነትን ሰጥቶታል (እንደ ጭቃ ርጥብ ብቻ ሳይሆን እንደ አቧራም ደረቅ ይሆናል።) እንደዚሁም መሬት በራሱ ብርሃን አመንጭ ወይም አንጸባራቂ አይደለም ሲል ጥቁርነትን ሰጥቶታል።  

ከዚህ በኋላ ግዙፍ ነገሮችን ሁሉ እንዴት ከነዚህ አራት ባሕርያት እንደተቀመሩ ያትታል። ለምሳሌ ፣ ፀሐይ፡ ከነፋስ እና ከእሳት (በእሳትነቷ ታቃጥላላች ፣ በነፋስነቷ ትንቀሳቀሳለች)፣ ጨረቃ፡ ከነፋስ እና ከውኃ (በነፋስነቷ ትንቀሳቀሳለች በውኃነቷ ታንጸባርቃለች)፣ የሰው ሥጋዊ ባሕርይ፡ ከአራቱም ባሕርያት።

ሥዕል1፡ ፀሐይ

ሥዕል 2፡ ጨረቃ

ሥዕል3፡ ሥጋ

ዋቢ መጻሕፍት

Dalton, J., Wollaston, W., & Thomson, T. (1893). Foundations of the Atomic Theory.

Einstein, A. (1905a). The Photoelectric Effect. Annalen der Physik.

መጽሐፈ አክሲማሮስ-ዘስድስቱ ዕለታት. (፲፱፻፺፱ ዕትም). ባሕር ዳር: አዘጋጅ እና አሳታሚ አባ ሰናይ ምስክር።.

የግርጌ ማስታወሻ


[1] መጠነ ቁሳቸውንና ሥፍራዊ ልኬታቸውን በመለካት ረገድ አንስታይን በብራውናዊ እንቅስቃሴ ላይ ያደረገው ሒሳባዊ ሐተታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል (Einstein, 1905a)። የነጠላ አተምን መጠን መወሰን አይቻልም።

[2] ብርሂት ፣ ቀናሲት

[3] ቀዳሚት ፣ ደማሪት

[4] ገለልቲት ፣ ዐልቢት

Leave a comment