በቅርቡ አንድ ተናጋሪ ስለ ሜታ ፊዚክስ እና ተያያዥ የሆኑ አጉራ ዘለል ልፈፋዎችን ሲያደርጉ ዐየሁ። የተለያዩ የዘመናዊ ፊዚካ ቃላት በየቦታው ጣል ጣል ይደረጋሉ። አልፎ አልፎ ሃይማኖታዊ ቃላት ይወረወራሉ ፣ ጥቅሶች ይጠቀሳሉ። እንዲህ ዐይነት አጉራ ዘለል ልፈፋዎች ሲበዙ ፣ በወቅቱ ማብረሻ ካልተበጀላቸው ማኅበረሰባዊ ውዥንብር ይፈጥራሉ። እንደዚህ ዐይነት ነገሮችንም አለምርመራ ለማኅበረሰቡ ማቅረብ ኃላፊነት የጎደለው ነው ብየ አስባለሁ።
ሜታ ፊዚክስ
የቀዳሚ መርሖችን ጉዳይ እና ሐሳባዊ የሆኑ ዕይታዎችን ፣ ስለ መሆን ፣ ማንነት ፣ ዕውቀት ፣ ጊዜ እና ቦታ ስለመሳሰሉ ይዘቶች የሚያትት የፍልስፍና ቅርንጫፍ ነው።
የዚህ ፍልስፍና ቀዳሚ ሐተታ በአሪስጣጣሊስ የተደረሰ ነው። ስሙን ያወጣው ግን አሪስጣጣሊስ ሳይሆን የአሪስጣጣሊስን ሥራዎች በአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቅልክ ስብስቦ የጠረዛቸው አንድሮኒከስ (Andronicus of Rhodes) የሚባል ሰው ነው። በጽርእ ቋንቋ ሜታ ማለት በኋላ ፣ ተከትሎ ማለት ነው። ስለዚህ የሜታ ፊዚክስ ቀጥተኛ ትርጉም ከፊዚካ በኋላ የሚል ነው። የአሪስጣጣሊስ ሥራዎች (ከሦስት ሺህ ገጽ በላይ ያለው) በድረገጽ ይገኛል። የተወሰኑትን ክፍሎች ቀደም ብየ ለማጥናት ዕድሉ የነበረኝ ቢሆንም ይኸን ክፍል በደመምሳው እንጅ አድምቸ አላነበብኩትም ነበር። ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሜታ ፊዚክስ ሥም በሀገራችን የሚደረጉ ዲስኩሮችን ስመለከት ጥቂት ነገር ለማለት ስለፈለግሁ ይዘቱን የተወሰነ ገረፍ ገረፍ አደረገሁት። ከዛሬ 2400 ዓመት በፊት የተደረሰ ፍልስፍናዊ ድርሰት ቢሆንም ቅሉ ብዙ በሳል እና ጥልቀት ያላቸው ፍልስፍናዊ ሐሳቦችን የያዘ ነው።
በግሪክ ቋንቋ ሶፊያ ማለት በእንግሊዘኛው wisdom በአማርኛ ምናልባት ጥበብ ሊሆን ይችላል። ፊሎ ማለት ደግሞ ፍቅር ማለት ነው። ስለዚህ ፊሎሶፊ (ፍልስፍና) የጥበብ ፍቅር ፣ አፍቅሮተ ጥበብ ተብሎ ሊተረጎም ይችል ይሆናል። አሪስጣጣሊስ ሶፊያ ቀዳሚ ምክንያቶችን (anitia) ወይም መርሖችን የሚመለከት የዕውቀት ዘርፍ ነው ይላል። ሜታ ፊዚክስም የሚያተኩረው እነዚህ ቀዳሚ (መሠረታዊ) ምክንያቶች ወይም መርሖች ላይ ለመድረስ የሚደረግ ሐተታ ላይ ነው። ይኸን የፍልስፍና ዘርፍ መሠረታዊነቱ ከሌሎች የፍልስፍና ዘርፎች ሁሉ የላቀ መሆኑን ለማመልከት አሪስጣጣሊስ ቀዳሚ ፍልስፍና ይለዋል።
አሪስጣጣሊስ በዘርፎች (Categories) ሐተታው ላይ የመሆን ነገሮችን መድቧል ፣ ከነዚህም ውስጥ ይዘት (ሥሪት) ፣ መጠን ፣ ቅስም እና ዝምድና ይገኙበታል። የነገር ይዘት (ሥሪት) መሠረታዊ እንጅ ጥገኛ አይደለም። ሌሎች የመሆን ምድቦች ግን በነገሩ ይዘት (ሥሪት) ላይ በአንድም በሌላም መልክ ጥገኛ ናቸው ፣ ከይዘቱ (ሥሪቱ) ውጭ ሕልውና የላቸውም። ለምሳሌ ቀለም በአካላት ላይ ፣ ዕውቀትም በነፍስ ላይ ጥገኛ ናቸው ከነዚህ መሠረታዊ ይዘቶች (ሥሪቶች) ውጭ የየራሳቸው ሕልውና የላቸውም። ስለዚህም የትኛውም መሆን ሄዶ ሄዶ የሆነ ይዘት (ሥሪት) ላይ የሚደርስ እና ይዘቱን ዋቢ የሚያደርግ መሆን አለበት። የሜታ ፊዚክስ ሐተታ ይኸን መሠረታዊ የነገሮች የመሆን ማዕከል የሆነን ይዘትን (ሥሪትን) በመበየን ላይ የሚያጠነጥን ነው።
ነገሩ ሐሳባዊ እንጅ ተግባራዊ አይደለም። በሥነሞገት የሚወጠር ፣ የሚያከራክር የሚያወያይ ነው እንጅ መተግበሪያ አይደለም “በሜታ ፊሲክስ እንዲህ ማድረግ ይቻላል” የሚል ንግግር እውነት ሊሆን አይችልም። አሪስጣጣሊስ በሜታ ፊዚክስ የሚመለከተው ስለተፈጥሮ መሠረታዊ ባሕርይ እንጅ ከተፈጥሮ በላይ ስለሆነ ነገርም አይደለም።
